×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
የህይወት ጥያቄዎች

በጭንቅ ስንከበብ እግዚአብሔር ወዴት ነው?

እግዚአብሔር ሆይ ወዴት ነህ?; ብላችሁ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ፣ እግዚአብሔርን ምነው ያላችሁባቸው ጉዳዮች በእርግጥ ምን ያህል ናቸው ?

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

በማሪሊን አዳምሰን

በእግዚአብሔር የምንታመነው በምን ያህል መጠን ነው? በገጠሙን ሁኔታዎች ሁሉ ፊታችንን ወደእርሱ እናቀናለንን… ሁኔታዎች ሲረጋጉ የምንሆነውን ያህል ቀውስ ሲገጥመን ያንኑ እናደርጋለን?

እግዚአብሔር ወዴት ነው?

እግዚአብሔር እኛ እንድናውቀው የሚሻ የፍጥረተ ዓለም ፈጣሪ ነው። እኛ ሁላችን በዚህ ያለነው በዚህ ምክንያት ነው። የእርሱን ብርታት፣ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ቅድስናና ርህሩኅነት እንድንለማመድና በእርሱም እንድንታመን የእርሱ መሻት ነው። ፈቃደኛ ለሆኑት ሁሉ ”ወደ እኔ ኑ”፤በማለት ይጣራል።

እርሱ እንደእኛ አይደለም፤ ነገ፤ በመጪው ሳምንት፤ በሚቀጥለው ዓመት፤ በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት የሚሆነውን ያውቃል። "ከመጀመሪያ የመጨረሻውን የምናገር እኔ እግዚአብሔር ነኝ ፣ እኔንም የሚመስል የለም" ይላል ኢሳ 46፡9 ። በዓለም ላይ ምን እንደሚሆን ያውቃል። ሊረዳችሁም ከእናንተ ጋር ይሆናል። እርሱ ”መጠጊያችንና ኃይላችን ባገኘንም በታላቅ መከራ ረዳታችን እንደሚሆን"1 ነግሮናል ። ነገር ግን እርሱን ከልባችን መሻት ይገባናል። ”ብትፈልጉኝ ታገኙኛላችሁ፣ በፍፁም ልባችሁ ካሻችሁኝ ታገኙኛላችሁ”2 ብሏል።

ይህ ማለት ግን እግዚአብሔርን የሚያውቁ አስቸጋሪ ወቅቶች አይደርሱባቸውም ማለት አይደለም። በፍጹም። የአሸባሪዎችን ጥቃት ለብዙዎች ጭንቅና ሞት ምክንያት ሲሆን እግዚአብሔርን የሚያውቁትም የዚያው ጭንቅ ሰለባዎች ይሆናለ።ነገር ግን የእግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር መሆን የሚያመጣላቸው ሰላምና ብርታት አለ። ከኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች አንዱ "በሁሉም እንጨነቃለን፣ ነገር ግን አንጠፋም፤ እናመነታለን፣ ነገር ግን ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን ግን አንጣልም፤ እንንገላታለን፣ ነገር ግን አንጠፋም"3 ሲል ገልጦታል። በሕይወታችን ልዩ ልዩ ችግሮች እንደሚገጥመን እውነታው ይነግረናል። ሆኖም፣ እግዚአብሔርን በማወቅ በውስጣቸው ስናልፍ የምንመለከታቸው ፍጹም በተለየ መንገድ ሲሆን ፈጽሞ የእኛ ባልሆነ ኃይልም እንጋፈጣቸዋለን። የትኛውም ችግር ለእግዚአብሔር ከአቅሙ በላይ ሆኖ አያውቅም። እኛን ከሚያንገላቱን ችግሮች ሁሉ ይበልጣል ስለዚህም ብቻችንን እንድንጋፈጣቸው አይተወንም።

የእግዚአብሔር ቃል "እግዚአብሔር መልካም ነው፣ በመከራም ቀን መሸሸጊያ ነው፣ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል"4 ይላል። "እግዚአብሔር ለሚጠሩት፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው፣ የሚፈሩትንም ከመልካም ነገር አያጎድላቸውም(የልባቸውን መሻት ይፈጽምላቸዋል)፣ ጩኸታቸውን ይሰማል ያድናቸዋልም"5 በማለትም ጨምሮ ይናገራል።

ኢየሱስ ለተከታዮቹ እነዚህን የሚያጽናኑ ቃላት ነገራቸው እንዲህ ሲል "በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም። የራስ ጠጉራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቆጠረ ነው ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው"6። በእውነት ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ፣ ማንም ሰው አድርጎ በማያውቀውና ሊያደርገው በማይችለው መንገድ ለእናንተ ግድ ይለዋል።

ሰቆቃና የእኛ ነፃ ፈቃድ

እግዚአብሔር የሰውን ዘር የፈጠረው ከነፃ ፈቃድ ጋር ነው። ይህም ማለት ከእርሱ ጋር ሕብረት እንዲኖረን አያስገድደንም ማለት ነው። እርሱን ወደጎን ተወት እንድናደርገው(እንድንክደው) እና ሌሎች ክፉ ስራዎችን እንድንሠራ መብት አለን ማለት ነው። አፍቃሪ እንድንሆን ሊያስገድደን ይችል ነበር። ግን ከእርሱ ጋር የሚኖረን ግንኙነት ምን ዐይነት የሚሆን ይመስላችኋል? በፍጹም ወዳጅነት ሊሆን አይችልም፣ ሊሆን የሚችለው በግድ የሚደረግና ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት መታዘዝ ብቻ ነው። እርሱ ግን ነፃ ፈቃድ ሰጥቶናል።

እንዲያው በተፈጥሮ፣ ከውስጥ ከነፍሳችን “እግዚአብሔር ሆይ፣ ነገሮች ይህንን ያህል(አሳዛኝ) እንዲሆኑ የምትተዋቸው እንዴት ነው?” ብለን እንጮሃለን።

እግዚአብሔር እንዴት ምላሽ እንዲሰጥ ነው የምንጠብቀው? የሰዎችን ተግባራት እንዲቆጣጠር ነው የምንሻው? በአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያት የሚያልቁት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ድረስ ብቻ እንዲሆን ነው የምንፈቅደው? በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ብቻ እንዲገደሉ እግዚአብሔር ቢፈቅድ የተሻለ ስሜት ይሰማን ይሆን? ወይስ እግዚአብሔር አንድ ሰው ብቻ እንዲሞት ቢፈቅድ? ሆኖም ግን እግዚአብሔር የአንድን ሰው ሞት እንኳን ቢከለክል፣ ነፃነት የሚባል ምርጫ አይኖረንም። ሰዎች እግዚአብሔርን ቸል ማለትን ይመርጣሉ፣ እግዚአብሔርን አሻፈረኝ ይላሉ፣ በራሳቸው መንገድም በመጓዝ በሌሎች ላይ ዘግናኝ ተግባራትን ይፈጽማሉ።

ሰቆቃና ዓላማችን

ይህች ፕላኔት ምቹ አይደለችም(ስጋት የሌለባት አይደለችም)። አንድ ሰው ሊተኩስብን ይችላል። ወይም በመኪና ልንገጭ እንችላለን። በአሸባሪዎች ጥቃት ምክንያትም ከፎቅ አራሳችንን ልንወረውር እንችላለን። በዚህች መሬት ብለን በምንጠራት አሰቃቂ ስፍራ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ተከትሎ ነገሮች በማይከናወኑበት ስፍራ ብዙ ነገር ሊደርስብን ይችላል።

ሆኖም፣ እግዚአብሔር በሰዎች ምህረት አይደገፍም፣ እንዲያውም በተቃራኒው እኛ በእርሱ ምህረት ስር እንሆናለን እንጂ። ይህ እግዚአብሔር ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብቶች ያሉበትን ፍጥረተ ዓለም “ይሁን” በሚሉ ጥቂት ቃላት የፈጠረ ነው7። ለኀይሉና ለጥበቡ ወሰን የለውም። ምንም እንኳን ፈጽሞ ልናሸንፋቸው የማይቻሉ ችግሮች ቢከብቡንም “እኔ የሥጋ ለባሽ ሁሉ አምላክ ነኝ፣ በውኑ ለእኔ የሚያቅተኝ ነገር አለን?”8 በማለት የሚያጽናና አስደናቂ ሁሉን ቻይ አምላክ አለን። ኃጢያት የሚቀናውን የሰው ዘር ነፃነት ይጠብቃል፣ ሆኖም ግን ፈቃዱን ይፈጽማል። እግዚአብሔር በግልጽ “ምክሬ ትጸናለች፣ ያሰብኩትንም ሁሉ እፈጽማለሁ”9 ይላል። ሕይወታችንን ለእርሱ ከሰጠን መጽናናትን ከእርሱ እንቀበላለን። “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል ለትሁታን ግን ጸጋን ይሰጣል”10

ሰቆቃ እግዚአብሔር አሁን የት ነው?

አብዛኞቻችን አይ፣ ሁላችንም ብዙ ጊዜ በእግዚአብሔርና በመንገዱ ላይ እናምጻለን። ከሌሎች ጋር በተለይም ከአሸባሪዎች ጋር ስናነፃፅር ራሳችንን ሰዎችን የምናከብርና የምንወድድ ነን ብለን እንቆጥራለን። ነገር ግን ልባችንን ክፍት አድርገን፣ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ብንገናኘው ልባችን በኃጢያት የተሞላ ሆኖ እናገኘዋለን። ወደ እግዚአብሔር በፀሎት ስንቀርብ፣ በሁሉ ደካሞች ሆነን እግዚአብሔር ሃሳቦቻችንን፣ ድርጊቶቻችንንና ራስ ወዳድነታችንን የሚያውቅ መሆኑን በመረዳት ትንፋሻችን ቁርጥ አይልምን? በአኗኗራችንና በልዩ ልዩ ተግባሮቻችን ራሳችንን ከእግዚአብሔር እናርቃለን። ያለ እርሱም ሕይወታችንን በግሩም ሁኔታ መምራት እንደምንችል እናስባለን። መጽሐፍ ቅዱስ “እኛ ሁላችን እንደሚጠፉ በጎች ነን፣ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ”11 ይላል።

ታዲያ ውጤቱ ምንድነው? ኃጢያታችን እኛን ከእግዚአብሔር ለይቶናል በአሁኑ ሕይወት ከምናየውም በበለጠ ሕይወታችንን አደጋ ውስጥ ጥሎታል። የኃጢያታችን ደሞዝ ሞት ነው፣ ይህም ለዘላለም ከእግዚአብሔር መለየት ነው። ሆኖም ግን፣ እግዚአብሔር ምህረት የምንቀበልበትንና እርሱን የምናውቅበትን መንገድ አዘጋጅቶልናል።

እግዚአብሔር የት ነው? የእግዚአብሔር ፍቅር

እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ወደ ምድር መጣ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወድዶአልና፤ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም የላከው በዓለም ለመፍረድ ሳይሆን፣ ዓለምን በእርሱ ለማዳን ነው።”12

በዚህ ምድር የሚገጥመንን ሕማምና ስቃይ እግዚአብሔር በሚገባ ያውቃል። ኢየሱስ የሚኖርበትን ምቹና ስጋት የሌለበትን ስፍራ ትቶ እኛ ወደምንኖርበት ከባድ አካባቢ መጣ። ኢየሱስ ደክሞታል፣ መራብና መጠማትን ያውቃል፣ ከሌሎች በደረሰበት ተቃውሞ ደርሶበታል። በቤተሰብና በቅርብ ጓደኞቹ መገለል ደርሶበታል። ኢየሱስ በየዕለቱ ፈታኝ ሁኔታዎችን ከማለፍ የዘለለ ብርቱ ነገር ገጥሞታል። ኢየሱስ፣ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ፣ በፍጹም ፈቃድ ኃጢያታችንን ሁሉ ወስዶ የኃጢያታችንንም ዕዳ ከፈለ። “ፍቅርም በዚህ ተፈጽሞአል፣ ሕይወቱን ስለእኛ አሳልፎ ሰጥቶአልና”13 በብርቱ ግርፋት ውስጥ አልፎአል፣ በስቃይ ጣዕር ሞቷል፣ በመስቀል ላይ በውርደት ተሰቃይቶ ሞቷል ስለዚህ ምህረትን አግኝተናል።

ኢየሱስ ከመሞቱ አስቀድሞ ተሰቅሎ እንደሚሞት ለሌሎች ተናግሯል። ከሦስት ቀናትም በኋላ ከሞት ተነስቶ ሕያው እንደሚሆን ተናገሯል። አንድ ቀን ስጋ ለብሼ እከሰታለሁ አላለም። (ይህን ብሎ ቢሆን ያደርገዋል ብሎ ማን ያምን ነበር?) ከተቀበረ ከሦስት ቀናት በኃላ መሰቀሉን ላዩ ሁሉ በአካል ሕያው ሆኖ እንደሚታያቸው ተናግሯል። በሦስተኛውም ቀን ኢየሱስ የተቀበረበት መቃብር ባዶ ሆኖ ተገኘ እናም ብዙ ሰዎች ሕያው ሆኖ እንዳዩትም መሰከሩ።

አሁን ለእኛ የዘላለም ሕይወት ሰጥቶናል። ይህ ለእኛ የተገባ አልነበረም። እርሱ ወደ ሕይወታችን እንዲገባ ስንለምነው የምንቀበለው ከእግዚአብሔር ለኛ የሚሰጥ ስጦታ ነው። የእግዚአብሔር ስጦታ በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው። ኃጢያታችንን በመናዘዝ ወደ እግዚአብሔር ብንመለስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ስጦታ እንቀበላለን። ነገሩ የተወሳሰበ ሳይሆን ግልጽ ነው።

“እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጥቶናል፣ ይህም ሕይወት በልጁ ነው። ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።”14 እርሱ ወደ እኛ ሕይወት ሊገባ ይሻል።

እግዚአብሔር የት ነው? የእግዚአብሔር እቅድ

የመንግስተ ሰማያትስ ጉዳይ? መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር “ዘላለማዊነትን በሰዎች ልብ ውስጥ አኖረ”15 ይለናል። ምናለባት በልባችን የተሻለችው አለም ምን እንደምትመስል እናውቃለን ማለት ነው።በጣም የምንወዳቸው ሰዎች ሞት በዚህ ዓለም በምንኖረው ሕይወት ውስጥ አንድ ችግር ያለ መሆኑን ይነግረናል። በነፍሳችን ውስጠኛ ማንነት ውስጥ ለመኖር የተሻለ ልብን ስብር ከሚያደርግ ችግርና ስቃይ የነፃ አንድ ስፍራ እንዳለ እንረዳለን። በእርግጠኝነት፣ እግዚአብሔር ለእኛ የተሻለ ስፍራ አዘጋጅቶልናል። ይህም ስፍራ የእርሱ ፈቃድ በሙላት የሚፈጸምበት የተለየ ሥርዓት ነው። በዚያ ዓለም እግዚአብሔር ከሰዎች ሁሉ ዐይን እንባን ያብሳል። በዚያ ልቅሶ፣ ስቃይና ሞት የለም። እግዚአብሔርም፣ መንፈሱ በሰዎች ውስጥ ይኖራል ከእንግዲህም ወዲያ ኃጢያትን አያደርጉም።

የአሸባሪዎች ጥቃት የተከሰቱባቸው ሁኔታዎች እጅግ አስፈሪ ናቸው። ኢየሱስ ለእናንተ ያዘጋጀውን ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ወዳጅነትን መመስረትን አሻፈረኝ ማለት ከዚያ እጅግ የከፋ ነው። ከዘላለም ሕይወት አንፃር ብቻ ሳይሆን በዚህ በምንኖርበት ሕይወት እግዚአብሔርን ከማወቅ አንፃር ምንም ግንኙነት አይኖረንም። የመኖራችን ዓላማ እርሱ ነው፣ የመጽናናታችን ምንጭም እርሱ ነው፣ ግራ በተጋባንባቸው ወቅቶች ጥበባችን ነው፣ ብርታትና ተስፋችንም እርሱ ነው። “እግዚአብሔር መልካም መሆኑን ቅመሱ እዩም፤ እርሱን መጠጊያው ያደረገ ሰው ምስጉን ነው።”16

እግዚአብሔር ምርኩዝ ነው የሚል አባባል አለ። ነገር ግን እርሱ ብቻ ሊተማመኑበት የሚገባ አምላክ ነው ቢባል አግባብ ይሆናል። ኢየሱስ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጣችሁ አይደለም። ልባችሁ አይጨነቅ፤ አይፍራም።”17 ብሏል። በሕይወት ዘመናቸው በኢየሱስ ላይ የተደገፉ ሰዎች፣ ሕይወታቸውን በዐለት ላይ እንደመሰረቱ ያረጋግጥላቸዋል። በዚህ በምትኖርበት ሕይወት የትኛውም ቀውስ ይምጣባችሁ እርሱ ያበረታችኋል።

እግዚአብሔር የት ነው? የእግዚአብሔር ልጅ

አሁን በምትገኙበት በየትኛውም ስፍራ ኢየሱስን ወደ ሕይወትህ መጋበዝ ትችላለህ።”ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔ ር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሣልጣንን ሰጣቸው”18 ወደ እግዚአብሔር መመለስ የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። ኢየሱስም “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም; ብሏል። “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ በሩንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እመጣለሁ”19 በማለት ጥሪውን ያቀርባል።

አሁን እግዚአብሔር ወደ ሕይወትህ እንዲመጣ ልትጠይቀው ትችላለህ። ይህንንም በፀሎት ተግባራዊ ልታደርገው ትችላለህ። ፀሎት ማለት በፍጹም ግልጽነትና እውነተኝነት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው። በዚህ ሰዓት ከዚህ በታች በተገለጸው ዐይነት የልብሕን በመንገር በግልጥነት ልትጠራው ትችላለህ።

“እግዚአብሔር ሆይ በልቤ ከአንተ ተለይቻለሁ፣ ያንንም ሁኔታ መለወጥ እሻለሁ። አንተን ማወቅም እፈልጋለሁ።ኢየሱስ ክርስቶስንና የእርሱን ይቅርታ በሕይወቴ መቀበል እፈልጋለሁ። ከአንተ ተለይቼ መኖር አልሻም። ከዚህ ዕለት አንስቶ የሕይወቴ ጌታ(አምላክ) ሁን። እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ።”

እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችሁ እንዲመጣ ከልብ ልመናችሁን ከለመናችሁ፣ ወደፊት ልትሹአቸው የሚገቡ በርካታ ነገሮች አሉ። እርሱን በማወቅ አሁን የምትኖሩት ሕይወት እርካታ የሞላበት እንዲሆን እግዚአብሔር ተስፋን ሰጥቶአችኋል። እግዚአብሔር የት ነው? እርሱ መኖሪያውን በእናንተ ውስጥ ለማድረግ ይሻል። የዘላለም ሕይወት ሰጥቶአችኋል(ይሰጣችኋል)።

በዚህ ዓለም ምንም ነገር በዙሪያችሁ ቢከሰት፣ እግዚአብሔር ስለ እናንተ በዚያ አለ። ምንም እንኳን ሰዎች የእግዚአብሔርን መንገድ መከተል ባይሹም፣ አሰቃቂ የሆኑ ሁኔታዎችንም የእርሱን ዓላማ ለማስፈፀም ይጠቀምባቸዋል። በዓለም ላይ የሚከናወኑ ድርጊቶችን ሁሉ እግዚአብሔር ይቆጣጠራል። እናንተ የእግዚአብሔር ከሆናችሁ፣ “እግዚአብሔርን ለሚወዱ እንደ አሳቡም ለተጠሩ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራላቸው እንዲደረግ እናውቃለን”20 በሚለው የተስፋ ቃል ላይ ማረፍ ትችላላችሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም።ልባችሁ አይታወክ አይፍራም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፣ ነገር ግን አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፊዋለሁ።”21 ብሏል። ፈጽሞም ላይረሳንና ላይተወንም ተስፋ ገብቶልናል።

እግዚአብሔርን ለማወቅና ለሕይወታችሁም ያለውን ፈቃዱን በማወቅ ለማደግ ይረዳችሁ ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ በማቴዎስ፣ በማርቆስ፣ በሉቃስና በዩሐንስ ወንጌላት የተፃፉትን አንብቡ።

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) መዝ 46፡1 (2) ኤር 29፡13 (3) 2ቆሮ 4:8-9 (4) ናሆ 1:7 (5) መዝ 145፡18-19 (6) ማቴ 10፡29-31 (7) መዝ 47፡8 (8) ኤር 32:27 (9) ኢሳ 46፡11 (10) ያዕ 4፡6 (11) ኢሳ 53፡6 (12) ዮሐ 3፡6-17 (13) 1ዮሐ 3፡16 (14) 1ዮሐ 5፡12 (15) መክ 3:11 (16) መዝ 31፡8 (17) ዮሐ 14:27 (18) ዮሐ 1፤12 (19) ዮሐ 14:6 (20) ሮሜ 8፡28 (21) ዮሐ 14፡27 16፡33


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More