በማሪሊን አዳምሰን
በምድር የሚኖር ሕይወት የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላትን ይጠይቃል። የመንጃ ፈቃድ ለመቀበል ፈተና ማለፍ ይጠይቃል። ሥራ ማግኘት ከፈለግህ ለሚፈለገው ሥራ ብቃት ያለህ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሊኖርህ ይገባል።
“ሀ”፣ ከዚያ ደግሞ “ለ” ጨምር። የተገባህ መሆኑን አረጋግጥ። መመዘኛውን ማሟላትህን አረጋግጥ። ተቀባይነት የምታገኝ መሆኑን አረጋግጥ።
እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የተቀበለህ መሆኑን የምታረጋግጠው በየትኛው ነጥበ ላይ ነው?
በምድር ላይ ከሚገጥሙህ ነገሮች ተቃራኒ በሆነ መንገድ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ግንኙነት በባዶ ቦታው ላይ አንተ በምትሞላው ነገር ላይ አይመሠረትም። “... ስላደረግሁ ተቀበለኝ”ነው።
የሚመሠረተው “ተቀብዬሃለሁ” “እንኳን ደህና መጣህልኝ ብዬሃለሁ” በሚለው በእግዚአብሔር ንግግር ነው።
ግብረ-ሰዶምም ሁን ወይንም ሌዝቢያን፣ መንታ ፆታ ይኑርህ ወይም ውዳገረድ ሁን ወይንም ጥያቄ ይኑርህ፣ እግዚአብሔር ጠላትህ አይደለም። እስካሁን ምንም እርምጃ ያልወሰድህ ከሆነ፣ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ግንኙነት መመሥረት ይፈልጋል። ይህንንም ስጦታ ለሁሉም ሰው ለማንኛውም ሰው ሰጥቷል።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ፣ ኢየሱስን ደጋግመው ያስቆጡ የነበሩ ቡድኖች… በራሳቸው ጽድቅ ይመኩ የነበሩ ሃይማኖተኞች እንደነበሩ ትመለከታላችሁ።
ኢየሱስ ከሁሉም ጋር ማለትም ከአመንዝራዎች እና ከወንጀለኞች ጋር ምን ችግር አልነበረበትም። ሆኖም፣ የሃይማኖት መሪዎች ደግመው ደጋግመው ኢየሱስን ያሳዝኑት ነበር። በፍርድ የተሞሉ፣ ግትር፣ ፍቅር የማያውቁና ግብዞች ሆነው አግኝቷቸው ነበር።
ምናልባት እነዚህን ቃላት ስትመለከቱ በእናንተ ላይ የሚፈርዱባችሁን እና ሚያሳዝኗችሁን ሰዎች ፈጥናችሁ ልታስቡ ትችሉ ይሆናል። ያ የኢየሱስን ልብ ይወክላልን? በፍፁም። ኢየሱስ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ ነው ያለው። ሰውን ሚያሳዝን ንግግር ታዲያ እንዴት ከዚህ ጋር ሊስማማ ይችላል? ፈፅሞ አይስማማም።
የተገለጠው የኢየሱስ ልብ ይህንን ይመስላል። “እናተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” ብሏል።1
በምድር የኖረ የትኛውም ሰው በማያደርገው መንገድ ኢየሱስ ሕይወትን በግሩም መንገድ ያብራራልሃል። ያም የተትተረፈረፈን ሕይወት እንዴት ልትኖር እንደምትችል ነው። በፍጥረተ ዓለሙ ውስጥ ያለውን ሁሉ የፈጠረ እርሱ ነው፣ ሆኖም ሰው ሆኗል፣ ስለዚህም እርሱን ደግሞም እግዚአብሔርን ልናውቀው እንችላለን።
ከኢየሱስ ጓደኞች አንዱ የነበረው፣ ዮሐንስ፣ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡ “እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበረና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።”2
“ጸጋ” የሚለው ቃል እኛ አዘውትረን የምንጠቀምበት ቃል አይደለም። የይገባኛል ጥያቄ ልናነሳ በማንችልበት መንገድ እግዚአብሔር መልካምነቱን ለእኛ አሳየን ማለት ነው። እጅግ ግራ አጋቢ በሆነ ሕይወት ውስጥ፣ ኢየሱስ መልካምነቱንና እውነቱን ሰጥቶናል።
በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ምን ለያስከፍል እንደሚችል ማሰብ እንኳን ሲቸግረኝ ኖሯል። እናንተም እንደኔው ሳትደነቁ አትቀሩም። ነገሩ እንዲህ ነው፡
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፣ በዓለም እንዲፈርድ አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።”3
አገኛችሁት? “በእርሱ የሚያምን ሁሉ።” በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ያገኛል። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በእርሱ አማካይነት ይድናል። በእርሱ ባመነ ላይ አይፈረድበትም።
እርሱ ከእኛ የሚጠብቀው … በእርሱ እንድናምን ብቻ ነው።
ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፣ “የእርሱ ወደሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።”4
እርሱ ነቢይ ወይም አስተማሪ ወይም የሃይማኖት መሪ ብቻ አልነበረም። እርሱን ማወቅ ማለት እግዚአብሔርን ማወቅ ማለት እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል። በእርሱ ማመን በእግዚአብሔር ማመን ነው። እርሱን ወደ መስቀል የወሰደው ይህ ነው። ተሳድበሃል ብለው ከሰሱት። ኢየሱስ “እግዚአብሔርን አባቴ ብሎ ሲጠራ፣ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አድርጓል” አሉ።5
ኢየሱስ ማረጋገጫ አሳይቷል። ኢየሱስ ሰብዓዊ ፍጡር ሊያደርግ የማይችለውን አድርጓል። ዐይነ-ስውራንን፣ መራመድ የማይችሉትን ወይም በህመም የሚሰቃዩትን ወዲያውኑ ፈውሷል።
ኢየሱስ ከዚያም የዘለለ ነገር አድርጓል። በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ እንደሚያዝ፣ እንደሚገረፍ፣ እና እንደሚሰቀል፣ ከሦስት ቀናትም በኋላ ከሞት እንደሚነሳ ተናግሯል። ይህ መቼም የማያጠራጥር ማስረጃ ነው። ደግሞ ትስጉትነቱ ተወግዶ በመናፍስታዊ ቋንቋ “በህልም ታዩኛላችሁ” አላለም። በፍፁም። ከተቀበረ ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ከሞት እነሣለሁ ነው ያለው።
ሮማውያኑ ይህንን ያውቁ ስለነበረ በኢየሱስ መቃብር ዙሪያ በርካታ ወታደሮችን አሰልፈው ነበር።
ሆኖም፣ ከተገረፈና በመስቀል ከተሰቀለ ከሦስት ቀናት በኋላ፣ ኢየሱስ በአካል መቃብሩን ፈንቅሎ ተነሣ። አካሉ በስፍራው አልነበረም፣ በስፍራው የተገኘው የተቀበረበት የከፈኑ ጨርቅ ብቻ ነበር። በቀጣዮቹ አርባ ቀናት ውስጥ ኢየሱስ በተለያዩ ወቅቶች በአካል ታይቶ ነበር። የክርስትና እምነት የተጀመረው እዚህ ነው። እኔ ነኝ ብሎ የተናገራቸውን ሁሉ ማድረግ የቻለ መሆኑን አሳይቷል። አምላክ ሥጋ መሆኑ፣ ከአብ ጋር እኩል መሆኑ።
ኢየሱስ ነገሩን በግልፅ አስቀምጦታል። “አባቴ በማንም ላይ አይፈርድም፣ ፍርድን ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል፣ ይህም አብን እንደሚያከብሩ ሁሉ ወልድንም ያከብሩት ዘንድ ነው። ወልድን የማያከብር የላከውን አብም አላከበረም። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሎቼን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለምን ሕይወት ያገኛል። ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ዳግመኛ ወደ ፍርድ አይመጣም።”6
አሁን የምትኖሩትን ሕይወት በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ መሆኑን በማወቅ ታልፉበታላችሁ።
እያንዳንዱ ሰው የፍቅር ርሃብ አለበት። ሰብዓዊ ፍቅር አስፈላጊ ነው። የሚወድድህ ሰው ሁሉ፣ የወዳጆችህ ፈቅር ግን ፍፁም አይደለም፣ ምክንያቱም ሰዎች ፍፁማን አይደሉምና።
እግዚአብሔር ግን በፍፁምነት ይወድድሃል። እርሱ የሚወድደን ማፍቀር ተፈጥሮው ስለሆነ ነው፣ እርሱም አይለዋወጥም፣ አያልቅምም።
ሁላችን ነገር የተደባለቀብን ነን። የእግዚአብሔርን ደረጃ ማሟላት ቀርቶ፣ የራሳችንንም ልክ እንኳን መኖር የተሳነን ነን። እግዚአብሔር የሚቀበለን ግን በፈፀምነው ተግባር አይደለም። ወደ እርሱ መጥተን፣ በእርሱ ስናምንና የሕይወታችን አምላክ እንዲሆን ስንጋብዘው ያን ጊዜ ይቀበለናል።
ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ኢየሱስ የገለጠው እንዲህ ነው፡
“አብ እንደወደደኝ ሁሉ እኔም ወደድኳችሁ፤ በፍቅሬ ኑሩ። እኔ የአባቴን ትእዛዝ ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር፣ እናንተም ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ደስታዬ በእናንተ እንዲሆንና ደስታችሁም ሙሉ እንዲሆን ይህን ነግሬአችኋለሁ። ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።”7
በሕይወታችሁ ያለ የትኛውም ትርጉም የሚሰጥ ግንኙነት በእናንተ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖ አለ። ልክ አይደለም? ይህ ነገር ለሁሉም ሰው እውነትነት አለው። ግንኙነቱ እየጠነከረ ሲሄድ፣ ተፅዕኖውም እያደገ ይሄዳል።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔርን ማወቅ ትርጉም የሚሰጥ ግንኙነት መሆኑ አስገራሚ አይሆንም። ሕይወትህን በፍቅሩ ደግሞም ለሕይወትህ ባለው ዓላማ መሠረት ይመራል። አንተም በራስህ የምትወስነው ውሳኔ የተጠበቀ ይሆናል። ነፃ ፈቃድህን ማንም አይነጥቅህም። ሕወትህን ነጥቆ እርሱ የሚፈልገውን አስገድዶ አያደርግብህም። ሆኖም ግን በጥበቡ፣ በበጎነቱ እና እግዚአብሔር ሰዎችንና ሕይወትን በሚያይበት አተያዩ ትማረካለህ።
እግዚአብሔር በማህበረሰብ ልፈፋ ላይ አይመሠረትም። ፍጥረተ-ዓለሙን የፈጠረ አምላክ፣ ማኅበረሰብ እንዲመራው አይጠብቅም፣ የሚጠብቅ ይመስልሃልን? ይህ እጅግ ደስ ያሰኛል። ያም ነጻነት ይሰጠኛል።
እኔ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ስጀምር፣ በሕይወቴ የሠራው ይህንን ይመስላል።
እኔ አምላክ የለሽ ነበርኩ። ለእኔ በእግዚአብሔር ማመን፣ ስለ እርሱ የሚተርከውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ በሕይወቴ አዲስ ምዕራፍ ነው። በመሠረቱ፣ የማይዘነጋ የመታሰቢ ሃውልት ነበር።
ኢየሱስ ወደ ሕይወቴ እንዲመጣ ከጋበዝሁት ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የቅርብ ጓደኛዬ “በሕይወትህ ለውጥ እንዳለ ታውቆሃልን?” ስትል ጠየቀችኝ። እኔም፣ “ምን ማለትሽ ነው?” አልኳት። እርሷም፣ “አሁን አሁን አንዳንድ ነገሮችን ሳጫውትህ አንተ ግን አታላግጥብኝም። ዝም ብለህ የምታደምጠኝ ይመስለኛል።” አለችኝ።
እፍረት ቢጤ ተሰማኝ። ማለቴ፣ የቅርብ ጓደኛዬ፣ ጨዋ ሰው ደግሞም እርሷ የምትናገረውን ብቻ የማደምጥ ሰው እንደሆንኩ ትነግረኝ ጀመር።
በሕይወቴ ካስተዋለችው ነገር የተነሳ ተገርማለች፣ ስለዚህ እርሷም ኢየሱስ ወደ ሕይወቷ እንደመጣ ጋበዘችው።
ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ስጀምር፣ ለእኔ ስላለው ፍቅር ተረዳሁ። ያም በጣም አስደነቀኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማነብባቸው ነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር እኔን ምን ያህል እንደወደደኝ የሚገልጡ ለእኔ በግሌ የተፃፉ ደብዳቤዎች ይመስሉኝ ነበር። (ሊለካ በማይችል መጠን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ይቆጣል ብዬ እያሰብሁ ነበር ያደግሁት።) ስለዚህ እግዚአብሔር እኛን ይወድዳል የሚለው ነገር ለእኔ አስደናቂ ነው።
ይህንን በመሰለ ጥልቀት የፍቅር ርሃብ ስሜቴ ሊረካ ሚችለው በእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እገምታለሁ፣ ያንን ስረዳም ስሜታዊ ዋስትናው የተጠበቀለት ሰው ሆንሁ። ከራሴ ይልቅ ይበልጥ ለሌሎች ማሰብና ግድ መሰኘት ጀመርሁ። ጭብጥ በሆነ መንገድ ጥሩ አድማጭና ጠንቃቃ ሰው ሆንሁ። ያደግሁበትንም የዘር አክራሪነት አስተዋልኩ።
እርሱ እንዲመራንና እንዲያስተምረን ስንፈቅድለት፣ “እውነትን ታውቃላችሁ፣ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” የሚለው ቃሉ እንደሚፈፀም ኢየሱስ ተስፋን ሰጥቷል።8
ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ስትጀምር፣ በአስተሳሰብህ ላይ ለውጥ ልታስተውል ትችላለህ፣ ወይም ተስፋህ የለመለመ ትሆናለህ፣ ወይም ስለሌሎች ያለህ አመለካከት ይቀየራል፣ ወይንም የጊዜ አጠቃቀምህ ይስተካከላል። ነገሩን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። እርሱን ስታውቀው ግን፣ በሕይወትህ ላይ ተፅእኖ ይፈጥራል። ኢየሱስን የሚከተል የትኛውንም ሰው ጠይቅ፣ እርሱን ማወቃቸው በሕይወታቸው ያመጣውን ተፅዕኖ ይነግሩሃል።
መንገዶችን እንድንመርጥም ትልቅ መሻትን ይፈጥርብናል። ይህን የሚያደርግበት አደራረጉ ግን የማይጠበቀ ነው። ነገሩ አሁን ልትከተል ሚገባህን አዲስ ትእዛዝ እንደመስጠት ዓይነት አይደለም። ነገሩ የራስ ጥረት ወይም ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ማድረግ አይደለም። ሃይማኖታዊ ቁርጠኝነትም አይደለም። ጉዳዩ የዝምድና ነው፣ ያም ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ወዳጅ መሆን ነው። ስለ እራሱና ስለ ሕይወት በግልህ የሚያስተምርህ እና የሚመራህ እግዚአብሔር ራሱ ነው። ና! ብለን ስንጋብዘው ወደ ሕይወታችን ይገባል። በውስጣዊ ማንነታችን ከልብ በሚዘልቅ መንገድ ውጫዊውንም አካትቶ በሕይወታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ኢየሱስ የሕይወትን ትርጉም ይበልጥ ያሳውቅሃል። ሌሎቸ ግንኙነቶች፣ ሥራዎች፣ ስፖርቶች እና መዝናኛዎች በጠቅላላ የማይዘነጋ ትውስታ አላቸው፣ ሁሉም ግን ወደ ሙላት የማያደርሱ ብልጭታዎች ናቸው። ከእነርሱ የምናገኘው እርካታ የተሟላ አይደለም። በምድር ያለ የትኛውም ነገር ይህን ማድረግ አይችልም።
እኛ ሁላችን ዘላቂና አስተማማኝ የሆነን ነገር በብርቱ እንራባለን። ኢየሱስም “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፣ በእኔም የሚያምን ከቶም አይጠማም።” ብሏል።9 ንግግሩንም “ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶውን ወደ ውጪ አላወጣውም።”9 ዘመኔን ሁሉ ሁልጊዜ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚያዋጣ የህይወት ፍልስፍና ሳፈላልግ ኖሬአለሁ። እግዚአብሔርን ሳውቅ፣ ፍለጋዬ አበቃ። እርሱም ሊታመን የሚገባው ሆኖ አገኘሁት።
ከእርሱ ጋር ያለህ ግንኙነት ሌሎች ከእርሱ ጋር ካላቸው ግንኙነት የተለየ ነው። ምክንያቱም አንተ የተለየ ልምምድ፣ ሃሳብ፣ ፍላጎት፣ ህልም እና መሻቶች ያሉህ ሰው ነህ። ወንጌላትን በማንበብ ኢየሱስ ከእያንዳንዱ ሰው ጋር እንደግለሰብ ያደርግ የነበረውን ግንኙነት ተመልከት።
ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ግንኙነት በሕይወት ላይ ከሚገጥሙህ ከባድ ፈተናዎች የምታመልጥበት መደበቂያ አይደለም። በገንዘብ እጥረት ጫና፣ በብርቱ ህመም፣ በአደጋ፣ በመሬት ነውጥ እና በግንኙነት ልብ ሰባሪ ክስተቶች ውስጥ፣ ወ.ዘ.ተ. ልታልፍ ትችል ይሆናል።
በዚህ ሕይወት መከራ የመኖሩ ነገር አያጠያይቅም። በመከራው ውስጥ ብቻህን ልታልፍ ትችላለህ። ወይም ደግሞ በመከራ መካከል የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ህልውናውንና የቅርብ ወዳጅነቱን በእርግጠኝነት ልታገኝ ትችላለህ።
ሌላው ማሳሰቢያ እነሆ። ስለ ሌሎች ግድ መሰኘትህን ለማሳደግ ምናልባት ፈታኝ ወደ ሆኑ እና መስዋዕትነትን ወደሚጠይቁ ሙያዎች ውስጥ ሊያስገባህ ይችል ይሆናል።
ከኢየሱስ ደቀመዛሙርት አብዛኞቹ (ደግሞም ዛሬም የኢየሱስ ተከታዮች ከሆኑት ብዙዎቹ) ፈታኝ በሆነ መከራ ውስጥ አልፈዋል። ለምሳሌ፣ ጳውሎስ ደጋግሞ ታስሯል፣ ተደብድቧል፣ ለቁጥር በሚያታክት መጠን ተገርፏል። በድንገት በቁጣ በተቀሰቀሰ ንቅናቄም ለሞት እስከሚደርስ በድንጋይ ተወግሯል። ብዙ ጊዜ መርከቡ ተሰባብሯል። ህይወቱን እስኪስት ድረስ በረካታ ቀናትን ያለ ምግብ ኖሯል።
የኢየሱስ ተከታዮች ቀላል ሕይወት እንደማይኖሩ ግልፅ ነው። ሆኖም ጳውሎስና ሌሎች አማኞች እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ፍቅር ያለ መናወጥ አፅንተው በመያዝ ዘልቀዋል።
ጳውሎስ፣ “በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት፣ ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።” ሲል ፅፏል።10
የሕይወት ጉዞህን በዕቅድ ልታስቀምጠው አትችልም። ግብረ-ሰዶማዊ፣ ሌዝቢያን፣ መንታ ፆታ፣ ወይም ወንደቃ ብትሆንም አለበለዚያም ከየትኛው ጎራ እንደሆንህ ጥርጣሬ ያለብህ ከሆንህ፣ ከፈቀድህለት ኢየሱስ ሕይወትህን ይመራል። ያም ከምታስበው እጅግ የሚበልጥ ነው። ኢየሱስ፣ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ የሚከተለኝ ይሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ብሏል።11
በሕወትህ ምንም አድርግ ምንም፣ ኢየሱስ ፍፁም ይቅር ብሎሃል። ኃጢአታችንን ቸል ብሎ አያልፈውም። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ራሱን ስለ እኛ መስዋዕት በማድረግ ዕዳችንን ከፍሏል።
ስለ አንተ የተሰዋልህ የምታውቀው አንድ ሰው አለን? ሊስተካከለው ምንም ላይኖር በሚችል መንገድ ኢየሱስ ያደረገው ይህንን ነው። አንተንም ያን ያህል ይወድድሃል። እርሱ ወደ ልብህ ሊገባና ከአንተም ጋር ግንኙነት ሊመሠርት ይፈልጋል።
እግዚአብሔርን ማወቅ ትፈልጋለህን? እስካሁን ያላደረግህ ከሆነ፣ ወደ ሕይወትህ እንዲገባ እንድትፈቅድለት አበረታታሃለሁ። እኛን ሊያረካን የሚችለው ግንኙነት ይህ ነው። ይህንን ሕይወት ያለ እርሱ ልንገፋው አንችልም።
በምትፈልጋቸው ቃላት ልታናግረው ትችላለህ። እገዛ የሚያስፈልግህ ከሆነ፣ ልትል ሚገባህ ነገር ናሙና ይኸውልህ፡
“ኢየሱስ፣ በአንተ አምናለሁ። ስለ እኔ በመሞትህ እና ከእኔም ጋር ግንኙነት በመመሥረትህ አመሰግንሃለሁ። አንተ የሕይወቴ አምላክ እንድትሆን እፈልጋለሁ፣ ላውቅህ፣ ፍቅርህን ላጣጥመው፣ እና አሁን ሕይወቴን እንድትመራው ልጠይቅህ እወዳለሁ።”
► | ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች) |
► | ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ ልጋብዘው እሻለሁ ፡ ስለዚህ ጉዳይ የበለጠ ብታስረዱኝ |
► | ጥያቄ አለኝ |
የግርጌ ማስታወሻ: (1) ማቴዎስ 11፡28-29 (2) ዮሐንስ 1፡16፣17 (3) ዮሐንስ 3፡16-18 (4) ዮሐንስ 1፡11-12 (5) ዮሐንስ 5፡18 (6) ዮሐንስ 5፡22-24 (7) ዮሐንስ 15፡9-12 (8) ዮሐንስ 8፡32 (9) ዮሐንስ 6፡35፣37 (10) ሮሜ 8፡37-39 (11) ዮሐንስ 8፡12