×
ፈልግ
ስለህይወት እና ስለእግዚአብሄር በነፃነት
 ጥያቄ የሚጠይቁበት ድረገጽ
እግዚአብሔርን ማወቅ

እግዚአብሔርን በግል ማወቅ

WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More PDF

እግዚዘብሔርን በግል ለማወቅ ምን ያስፈልግሀል? የመብረቅ ብልጭታ? ጥብቅ ኃይማኖታዊ ስርዓት? የተሻልክ ሰው ሆኖ መገኘት? አንዳቸውም እነደ ቅደመ ሆኔታ አያስፈልጉህም። እግዚአብሔር እርሱን ለማወቅ የሚያስፈልገንን መፅሐፍ ቅዱስ ላይ በግልፅ አስቀምጦልናል።

ማንኛውም ነገር ደንብና ስርዓት አለው። ሰው የሠራቸው ነገሮች ሰው ሰራሽ ስርዓት እንዳላቸው ሁሉ እግዚአብሔር የፈጠራቸው ነገሮች ደግም የተፈጥሮ ሕግጋት አሏቸው።

እነዲሁም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስኑ አራት መንፈሳዊ ሕጎች አሉ። መርሆች ብለህም ልትወስዳቸው ትችላለህ።


የመጀመርያው ሕግ
እግዚአብሔር ይወድሃል ስለዚህም ለሕይወትህ አስደናቂ ዕቅድ አዘጋጅቶልሃል።

የእግዚአብሔር ፍቅር
“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ አለሙን እንዲሁ ወዶአልና።”1

የእግዚአብሔር ዕቅድ
ክርስቶስ እንዲህ አለ፡-
“እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።”2

ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ይህንን መሉና አርኪ
ሕይወት አልተለማመዱም ምክንያቱም . . .


ሁለተኛው ሕግ
ሰው ኃጢአተኛ ነው። በዚህም ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይቷል። ስለዚህም የእግዚአብሔርን ፍቅርና ዕቅድ ማወቅና በሕይወቱ መለማመድ አይችልም።

ሰው ኃጥአተኛ ነው
“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።”3

እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ከእርሱ ጋር የቀረበ ግንኙነት በመመስረት በደስታ እንዲኖር ነበር።ነገር ግን ሰው በራሱ መንገድ ለመጓዝ በመምረጡ ግንኙነታቸው ተቋረጠ። በራሳችን መንገድ ስንጓዝ ለእግዚአብሔር የማንታዘዝና ለርሱም ግድ የሌለን እንሆናለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አይነቱን አስተሳሰብ ነው ኃጢአት ብሎ የሚጠራው።

“እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ።”4

ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቷል ሰዎች
“የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና”5 ይህም ሞት በመንፈስ ከእግዚአብሔር መለየት ማለት ነው።

ይህ ስዕል የሚያሳው እግዚአብሔር ቅዱስ ሰው ደግሞ ኃጢአተኛ በመሆኑ በመካከላቸው ትልቅ መለያየት መኖሩን ነው። ቀስቶቹ የሚያመለክቱት ሰው በራሱ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ለመድረስ እንዴት እንደሚጥር ነው። ለምሳሌ፡- የሃይማኖት ስርአቶችን በመፈፀም፣ ቤተክርስትያን ሳያቋርጥ በመመላለስ፣ መልካምን ስራ በመስራት፣ ሰውን ባለመጉዳት፣ወ.ዘ.ተ. ነገር ግን ሰውን ጥረቱ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርበው አልቻለም።

ሦስተኛው ህግ ሰው ወደ እግዚአብሔር
የሚደርስበትን ብቸኛ ሕግ ያሳየናል . . .


ሦስተኛው ሕግ
ሰው ወደ እግዚአብሔር ሊደርስ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ስለ እኛ ሞቷል። ስለዚህም ሰው በእርሱ በኩል የእግዚአብሔርን ፍቅርና ዕቅድ ሊያውቅና ሊለማመድ ይችላል።

እርሱ በእኛ ምትክ ሞተ
‹‹ነገር ግን ገና ኃጢያተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።››6

ከሞት ተነስቷል
‹‹…ክርስቶስ ስለ ኃጢያታችን ሞተ ተቀበረም መጽሐፍ እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፣ …››7

እርሱ ብቸኛ መንገድ ነው፡-
ኢየሱስ እንዲህ አለ፡-
‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም››8

ይህ ስዕል የሚያሳየው እኛን ወደ ራሱ ሊመልሰን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ነው። ይህንንም ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ ስለእኛ እንዲሞት በመላክ ፈጽሞታል። ከዚህም የተነሳ ሁላችንም በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር መድረስ እንችላለን።


ነገር ግን እነዚህን ሦስት ሕጎች ብቻ ማወቅ በቂ አይደለም . . .


አራተኛው ሕግ
እያንዳንዳችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛችንና እንደ ጌታችን ልንቀበለው ይገባናል። ከዚያም የእግዚአብሔርን ፍቅርና ዕቅድ በሕይወታችን ልናውቅና ልንለማመድ እንችላለን።

ክርስቶስን ልንቀበለው ይገባናል
‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው››9

ክርስቶስን በእምነት ልንቀበለው ይገባል
‹‹ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም››10

በግላችን ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን በመጋበዝ ልንቀበለው ይገባል
ክርስቶስ እንዲህ ይላል፡-
‹‹እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል››11

ክርስቶስን መቀበል የሚከተሉትን ያጠቃልላል
- ኃጢያተኛ መሆናችንን ማወቅና ከኃጢያታችን ለመመለስ በመወሰን ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት

- ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢያታችንን ይቅር እንደሚልና ወደ ሕይወታችንም እንደሚመጣ ማመን

- ክርስቶስ በእኛ ውስጥ እንዲኖር መፍቀድና እርሱን ማሳየት


እነዚህ ሁለት ክቦች ሁለት አይነት ሕይወት ይወክላሉ፡-

በእኔነት ቁጥጥር ስር ያለ ሕይወት
ይህ ሰው የራሱን ሕይወት የሚቆጣጠረው ራሱ ነው። ክርስቶስ እስከ አሁንም ድረስ ከሕይወቱ ውጪ ነው ሕይወቱን በተለያየ አቅጣጫ የሚመራው ራሱ ነው ውጤቱም ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ማጣት ነው።

በክርስቶስ ቁጥጥር ያለ ሕይወት
የዚህ ሰው ሕይወት ተቆጣጣሪ ክርስቶስ ነው። በማንኛውም አቅጣጫ ክርስቶስ ሕይወቱን እንዲቆጣጠርለት ፈቅዷል ውጤቱም ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም መፍጠር ነው።


- የትኛው ክብ ሕይወትህን ይወክላል?
- ሕይወትህ የትኛውን ክብ እንዲመስል ትፈልጋለህ?


አሁኑኑ ክርስቶስን በእምነት ልትቀበል ትችላለህ

ከርስቶስን እንደግል አዳኝህና ጌታህ አድርገህ መቀበል የምትችለው በፀሎት ወደ ሕይወትህ እንዲመጣ በመጋበዝና በቃሉ እንደተናገረው እንደሚያደርግ በእርሱ በመታመን ነው። እግዚአብሔር ልብህን ስለሚያውቅ ልታታልለው አትችልም። ስለዚህ ፀሎትህ ከልብ የመነጨ መሆን አለበት።


እንዲህ ልትፀልይ ትችላለህ

‹‹ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ አንተን በግሌ ለማወቅ እፈልጋለሁ። ስለ ኃጢያቴ በመስቀል ላይ ስለሞትክልኝ አመሰግንሃለሁ። አሁን ልቤን ከፍቼ አዳኜና ጌታዬ አድርጌ እቀበልሃለሁ። ኃጢያቴን ሁሉ ይቅር ስላልከኝና የዘላለም ሕይወት ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፤፤ በሕይወቴ ዙፋን ላይ ሆነህ ግዛኝ አንተ የምትፈልገው ዓይነት ሰው አድርገኝ። አሜን!››

- ይህን ፀሎት ልትፀልይ ትወዳለህን?

- ፈቃደኛ ሆነህ አሁኑኑ ብትፀልይ በሰጠው ተስፋ መሰረት ክርስቶስ ወደ ሕይወትህ ይመጣል።

 ኢየሱስን ወደ ሕይወቴ እንዲገባ ጋበዝኩት (ተጨማሪ ሀሳቦች)
 ጥያቄ አለኝ

የግርጌ ማስታወሻ: (1) ዮሐ 3፡16 (2) ዮሐ 10፡10 (3) ሮሜ 3፡23 (4) ኢሳ 53፡6 (5) ሮሜ 6፡23 (6) ሮሜ. 5፡8 (7) 1ኛ ቆሮ. 15፡3-5 (8) ዩሐ› 14፡6 (9) ዩሐ.1፡12 (10) ኤፌ. 2፡8-9 (11) ራዕ. 3፡20


ሼር ያድርጉ
WhatsApp Share Facebook Share Twitter Share Share by Email More